Jul 27 / ብሩክቲ

ልጆች እና አካባቢያዊ ተጽዕኖ

የልጆች ማህበራዊ እና ስሜታዊ ክህሎት፡ ልጆች እና አካባቢያዊ ተጽዕኖ


የልጆችን ማህበራዊ ብሎም ስሜታዊ ዕድገታቸውን ለማጐልበት በልጆች አጠገብ ያለ ሰው ሁሉ ሀላፊነት አለበት። ይህን ስንል ከወላጆች እና አሳዳጊዎች ጀምሮ የቤተሰብ አባላት፣ አቻ ጓደኞቻቸው፣ በዙሪያቸው ሰዓትን ከእነርሱ ጋር የሚጋሩ ሰዎች በሙሉ እና የሚያድጉበት አካባቢ በራሱ የልጆችን ማህበራዊ ብሎም ስሜታዊ ክህሎት ለማዳበር ትልቅ ተጽዕኖ አላቸው። ልጆች ከሚያዩት እና ከሚሰሙት ተነስተው ባህሪያቸውን ይቀርጻሉ። ይህም የሚሆነው የአዕምሯዊ ዕድገታቸውን ተከትሎ ነው። ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አንድን ነገር አይተው ወይም ሰምተው ለማድረግ ወይም እንደ ሀሳብ የመቀበል ዕድላቸው ሰፊ ነው። አስተውላቸሁ ከሆነ ብዙ ጊዜ ልጆች ጠያቂ ናቸው። ይህ ጠያቂነታቸው የመጣው ለነገሮች አዲስ ከመሆናቸው እና ለማወቅ ካላቸው ጉጉት ነው። ይህን እንደ ወላጅ እና አሳዳጊ እንደ ጥሩ እድል ልንጠቀምበት ይገባል። 
ልጆች የተወለዱት ሰፊ በሆነ አካባቢ ነው። ይህ ሰፊ የሆነው አካባቢም በተለያዩ ነገሮች የተሞላ ነው። የተለያዩ ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ሁነቶች እንዲሁም አካባቢያችን ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ የተሞላ ነው። በልጆች ዙሪያ ያሉት እነዚህ ነገሮች በልጆች እድገት እና በአጠቃላይ አኗኗራቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ እንዳላቸው ይታመናል። ተመራማሪዎች እንደሚያመለከቱት ከሆነ፣ አብዛኛው ባህሪያችን ከግንኙነታችን ዘይቤ ጀምሮ እስከ የእውቀት (ኮግኒቲቭ) ክህሎት ድረስ ባለው የቅርብ አካባቢያችን ተጽዕኖ ይደርስበታል። ልጆች በአካባቢያቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። ልጆች የሚያዩትን ሰው ለመምሰል የሚሞክሩበትን መንገድ አስተውላችኋል? ወይም ልጅዎ እምነቶቹን ከአናንተ እና ከምትኖሩበት ማህበረሰብ ሲወስዱ አይተችሁ ታውቃላችሁ? አዎ! ልጆች በአካባቢያቸው ውስጥ ሁልጊዜ የሆነ ነገር እየያዙ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። ይህም ወደ ማህበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታቸው ይመጣል። ህጻናት በለጋ እድሜያቸው ከሚያዳብሩዋቸው ዋና ዋና ማህበራዊ እና ስሜታዊ ክህሎቶች መካከል፡- ስሜትን መቆጣጠር፣ ከሌሎች ጋር መጋራት እና መመሪያዎችን መከተል ነው። እነዚህ ክህሎቶች ለልጆች ጤናማ እድገት አስፈላጊ ናቸው። ህጻናትም ከአካባቢያቸው በሚደርስባቸው አዎንታዊ ተጽዕኖዎች እነዚህ ችሎታዎች እንደሚያዳብሩ ይታመናል። አካባቢ እና የልጆች እድገት በጣም የተያያዙ ነገሮች ናቸው። ልጆች የሚቀረጹት በዙሪያቸው ያሉትን ነገሮች በሚያዩበት መንገድ ነው። ስለዚህ ወላጆች እና አሳዳጊዎች የልጆችን ማህበራዊ እና ስሜታዊ ችሎታቸውን እያሳደጉ ልጆችን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የልጆችን ማህበራዊ እና ስሜታዊ እድገት ለመገንባት አዎንታዊ አካባቢ ቁልፍ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ ሲሄዱ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ፣ በቋንቋ እንዲሁም በጤና የዕድገት ዙሪያ ውስጥ ብዙ ለውጦችን እያሳዩ ይሄዳሉ። እነዚህ ለውጦች ለልጆች የወደፊት የአኗኗር ሁኔታ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍቱ ናቸው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ወላጆች እና የቤተሰብ አባላት በልጃቸው ዙሪያ ያለው አካባቢ ደስተኛ፣ ምቹ እና አዎንታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ከልጆችዎ ጋር ጥሩ የሆነ መስተጋብር ያድርጉ። ከልጆችዎ ጋር ብዙ በተግባቡ ቁጥር ወደፊት የልጆችዎ የተግባቦት ችሎታዎች የተሻለ ይሆናል። ንቁ መስተጋብር የልጆችን የአዕምሮ እድገት ያበረታታል። አዎንታዊ እና ጤናማ አካባቢ ለልጅዎ እድገት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ይህ ልምምድ መቀጠል አለበት። በመሆኑም ንጹህ፣ ጤናማ እና ለዕድገት ምቹ የሆነን አካባቢ በመፍጠር የልጆችን ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ ይቻላል። ይህም የሚሆነው በዋናነት ወላጆች እና አሳዳጊዎች ለልጆቻቸው በሚፈጥሩት ምቹ የሆነ እና ጤናማ አካባቢ ነው።